በናኖ ቴክኖሎጂ የሕክምና ተዐምር

የሰው ልጅ በእለት ተእለት ሕይወቱ በርካታ ነገሮችን አስቦበትም ይሁን ሳያስበው የሚያጋጥሙት ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንደኛው የጤና መታወክ ነው። በዓለም ላይ በየቀኑ በርካታ ሰዎች የጤና መታወክ የሚገጥማቸው ሲሆን ከ4 ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት የማያገኝ ነው። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች መጠቀስ የሚችሉ ቢሆንም ህክምና በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ መሰጠቱ ወይም በበቂ ሁኔታ አለመዳረሱ ግን ዋነኛ መንስዔ ተደርጎ ይወሰዳል።

አንድ ታማሚ በቤት ውስጥ ሆኖ ቢያንስ ቢያንስ ህመሙን በሚገባ ማወቅ ያለበት ሲሆን ካለው የህክምና መሳሪያ ውስንነት የተነሳ የተራራቁ የህክምና መሳሪያዎች ወደሚገኙበት ውድና ትላልቅ ሆስፒታሎች ለመሄድ ይገደዳል።

ዶክተር አኒታ ጎኤል በናኖባዮሲም ተቋም ውስጥ ፊዚክስን፣ ባዮ ሜዲሰንን እና ናኖ ቴክኖሎጂን በማጣመር በእሳቸው አጠራር ናኖ-ባዮ-ፊዚክስ ላይ ከ20 ዓመት በላይ ጥናት አድርገዋል። በተለይም ደግሞ ዲኤንኤ ላይ የሚገኙ ተከታታይ መረጃዎችን ማንበብና መፃፍ የሚችሉ ናኖ ማሽኖች ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር አድርገዋል። እነዚህ ማሽኖች በጣም ትናንሽ ሞለኪዩልን በመቅዳትና ዲኤንኤ ላይ የተቀመጡ መረጃዎችን ማንበብና ለሰው ልጅ በሚገባው ቋንቋ መረጃውን መተርጎም ይችላሉ።

ዶክተር አኒታ ከብዙ ጊዜ ጥናትና ምርምር በኋላ እንደ ትራይኮርደር ያለ መሳሪያ የፈጠሩ ሲሆን በተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች የሚሰሩ ስራዎችን በዚህ ማሽን ብቻ ማከናወን እንደሚቻል ገልፀዋል። በዚህ ማሽን ላይ የሚሰሩት አፕሊኬሽኖች ለጊዜው ትኩረታቸውን ያደረጉት በርካታ የኅብረተሰቡን ክፍል እያጠቁ ያሉ በሽታዎች ላይነው። ለምሳሌ በኢቦላ የተያዘ ሰው ምልክቶች ሳይታዩበት ነገር ግን በሽታው በደም ውስጥ ካለ ይሄ ማሽን ላይ በሚደረገው ምርመራ መጠቆም ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ 6 ወር ያህል የሚወስድን የHIV ምርመራ በደቂቃዎች ውስጥ መከወን ይችላል።

ዶክተር አኒታ ስለዚህ መሳርያ ሲገልፁም "ይህ መሳሪያ ታዲያ የህክምናውን ዘርፍ በእጅጉ ከማሳደጉም በላይ የተወሰነ ቦታ ብቻ የነበረው የህክምና አገልግሎት በሰፊው እንዲበታተን፣ ከዛም አልፎ በየግል ተደራሽ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል" ብለዋል።